ማህበራዊ ጤና መድህን ሊጀምር ነው::
በመንግሥትና በግል ድርጅቶች ተቀጥረው በመሥራት ላይ የሚገኙ ሠራተኞችን የሚያቅፈው ማኅበራዊ የጤና መድኅን አገልግሎትን በ2015 ለመጀመር እቅድ እንዳለው የኢትዮጵያ የጤና መድኅን አገልግሎት አስታወቀ።
በአገር ዐቀፍ ደረጃ እስካሁን በስፋት የተከወነው ማኅበረሰብ ዐቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት ሲሆን፣ በዚህ አገልግሎትም ከአገሪቷ ወረዳዎች መካከል 84 በመቶውን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አዲስ ማለዳ ከአገልግሎቱ ካገኘችው ሪፖርት ተመልክታለች። አገልግሎቱን የሚጠቀሙ የቤተሰብ ምጣኔም 66 በመቶ መድረሱ በአገልግሎቱ ሪፖርት ላይ ተመላክቷል።
ይህ የማኅበረሰብ ዐቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት መደበኛ ወርሀዊ ገቢ የሌላቸውን ቤተሰቦች የሚያቅፍ ሲሆን፣ ከተጀመረም 11 ዓመታትን አስቆጥሯል። ይሁንና ከዚሁ የማኅበረሰብ ዐቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት መጀመር 11 ዓመታትን ዘግይቶ ማኅበራዊ የጤና መድኅን አገልግሎት በዚህ የበጀት ዓመት ለመጀመር አገልግሎቱ አቅድ ይዟል።
በማኅበራዊ የጤና መድኅን አገልግሎቱ ዙሪያ ከዚህ በፊት ውይይት ሲደረግ ጥያቄ አስነስቶ የነበረው ከሠራተኞች የወር ገቢ ተቆራጭ የሚሆነው መዋጮ በመንግሥት ውሳኔ የሚሰጥበት ሲሆን፣ ይህ ውሳኔ ከተወሰነና መንግሥት በዚህ ቀን ይጀመር ባለበት ሰዓት አገልግሎቱን ለመጀመር የኢትዮጵያ የጤና መድኅን አገልግሎት ዝግጁ መሆኑ ታውቋል።
ቀድሞ በተጀመረው የማኅበረሰብ ዐቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎትም በአገር ደረጃ 3 ሺሕ 165 የጤና ተቋማት ጋር ውል የተፈጸመ ሲሆን፣ ከዚህም መካከል 2 ሺሕ 825 ጤና ጣቢያዎችና 340 ሆስፒታሎች ይገኙበታል። እነዚህ ተቋማትም በዚህ ዓመት ለሚጀመረው ማኅበራዊ የጤና መድኅን አገልግሎትም አገልግሎታቸውን የሚያቀርቡ ይሆናል።
በዚሁ የማኅበረሰብ ዐቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት ዓመታዊ የሆነ ክፍያ የሚከፍል ሲሆን፣ አንዴ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆነ ቤተሰብ በየዓመቱ የአባልነት እድሳት ያስፈልገዋል። ዓመታዊው የእድሳት ምጣኔ 83 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ይህንን የእድሳት ምጣኔም ከፍ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
የማኅበረሰብ ዐቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት ዓመታዊ መዋጮን መሸፈን ለማይችሉ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ቤተሰቦች መዋጮው በመንግሥት የተሸፈነላቸው ሲሆን፣ በዚህም ከ7 ሚሊዮን በላይ ግለሰቦች ተጠቃሚ እንደሆኑ በአገልግሎቱ ሪፖርት ላይ ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ የጤና መድኅን አገልግሎት አሁን በመስጠት ላይ ያለውን የማኅበረሰብ ዐቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎትና በዚህ ዓመት ለመጀመር ላሰበው የማኅበራዊ የጤና መድኅን አገልግሎቶችን ለማሳለጥና የተቋሙን የመረጃ አያያዝ ሥርዓት በማዘመን ዲጂታላይዜሽንን ለማጠናከር እንደሚሠራም ለማወቅ ተችሏል።
በመንግሥት ሆስፒታሎች ላይ ተግባራዊ የሚደረገውን የሕክምና አገልግሎት የዋጋ ተመንንም በማስጠናትና በማስተቸት ለሚመለከታቸው አካላት በማስተላለፍ አስፈላጊ የሆኑ ማሻሻያዎችም እንደሚደረጉ ታውቋል።
እስካሁን ድረስ በማኅበረሰብ ዐቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት 9.8 ሚሊዮን አባወራና እማወራዎችን ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፣ በዚህም 43 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ ተጠቃሚ መሆኑን በአገልግሎቱ ሪፖርት ተመላክቷል።
በዚህ ዓመት በሚጀመረው ማኅበራዊ የጤና መድኅን አገልግሎትም በርካታ ሕዝብ ተጠቃሚ እንደሚሆን ሲጠበቅ፣ በዚሁ ምክንያት አገራዊ የጤና መድኅን ሽፋንም ከፍ እንደሚል ይጠበቃል። የጤና መድኅን አገልግሎት በ2003 ዐስራ ሦስት ወረዳዎችን በማቀፍና የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኀን ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻል ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ የማኅበራዊ የጤና መድኅን አገልግሎት ግን በተለያዩ ምክንያቶች መጀመር ሳይችል መቆየቱ የሚታወስ ነው።
ዘገባው የ አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ነው::
Leave a Reply